ኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችን ለአገራችሁ ስለተዋደቃችሁ አመሰግናለሁ አለች

ታኅሣሥ 20 2014 (ዋልታ) ዲያስፖራው የአገሩ ጉዳይ መሪ በመሆን በዓለም አደባባይ ተቃውሞውን ሲያሰማ በመቆየቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አመሰገኑ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል::
አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የጀመሩትን ሴራ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ በበቃ ንቅናቄ እርቃኑን አስቀርተውታል፡፡ ለዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን ችረዋል::
አሸባሪው ትሕነግም ከተጠነሰሰበት ኢትዮጵያን የመበታተን ትልም በመነሳት በከፈተው ጦርነት በርካታ ንፁሀንን መጨፍጨፉን፣ ከቀያቸውና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡
ይህን ጥቁር ጠባሳ ለማከም የወገን ድጋፍ እና አለሁ ባይነት አስፈላጊ በመሆኑ ዲያስፖራው በዚህ በጎ ምግባር እንዲሳተፍ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኩል መዲናዋ በፀጥታ እክል ውስጥ ነች በሚል የሚነዛውን የሀሰተኛ መረጃ በአካል በመገኘት ለዓለም እውነታውን የምታሳዩበት ነው ብለዋል፡፡
በሄብሮን ዋልታው