ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ19 ሚሊዮን ዩሮ የዕርዳታ ስምምነት ተፈራረሙ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግሥታት መካከል የ19 ሚሊዮን ዩሮ የዕርዳታ ስምምነት ተፈረመ፡፡
የዕርዳታ ስምምነቱ 19 ሚሊየን ዩሮ ወይንም 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሲሆን የፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከናወኑ ሦስት የተለያዩ ፕሮጀክቶች በገንዘብ የሚደግፍበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያው ፕሮጀክት የ 8 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ለመጠገንና ለመንከባከብ የሚያስችል እንዲሁም ቅርሶቹ ማራኪ እንዲሆኑ ያግዛል ተብሏል፡፡
ሁለተኛው ፕሮጀክት የ10 ሚለየን ዩሮ ድጋፍ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይልን የሰራተኛውን ክህሎት በማሳደግ የተቋሙን ውጤታማነትን ለማጠናከርና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ይህን ለማድረግ እንዲቻል የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስገነባውን የስልጠና ተቋም ግንባታና የውስጥ መገልገያ መሳሪያዎች ለማሟላትም የሚውል የፕሮጀክት ድጋፍ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻው ፕሮጀክት የአንድ ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ሲሆን በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራትን ኤጀንሲን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን የማኅበራቱን አቅም በመገንባትና በማጠናከር ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያግዛል ነው የተባለው፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰውና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ መንግሥት ልማት ድርጅት ኃላፊ ቫሌሪ ቲአዎ የፈረንሳይ አምባሳደር በኢትዮጵያ ሬሚ ማስቹዌክስ በተገኙበት ፈርመውታል፡፡