ሀገረ ኢትዮጵያ ቁመቷ ተለክቶ ወርዷ ተሰፍቶ ከተሰጠችን ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
በነዚህ ዘመናት ቁመቷን ቆራርጠው ወርዷን ሸርሽረው መሃሏን ሊያፈራርሱ የሚሹ ብዙዎች ቢነሱም የቁርጥ ቀን ልጆቿ ሃሳብን በሃሳብ፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ሃይልን በመግባባት አለፍ ሲልም እንዳመጣጡ እያስተናገዱ ሃገርን ከባህሏ፣ ማንነቷ እና ክብሯ ጋር ማስቀጠል ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዘመናትን ባስተናገደው ታሪኳ የአለም ግንባር ቀደም የስልጣኔ ምንጭ፣ የጭቆናና የግፍ ማብቂያ የብስራት ደወል የነጻነት ፈር ቀዳጅ ብትሆንም ብዙ ውጣ ውረድን ያየች፣ ክቡር ልጆቿን በየጦር ሜዳው የሰዋች እና የደም ዋጋ የከፈለች መሆኗ ይዘከርላታል፡፡
በርካታ አርበኞቿ በቆራጥነት የተዋደቁበት፣ ከገድሏ የደመቀችበት፣ በጀብዷ የምትደነቅበት እና ፈተናዋ የጸናባት ታሪኳ በተለያዩ ዘመናት በየካቲት ወር መሆኑን ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ደፋሪዎቿን ያሳፈረችበት፣ ስሟን በአለም የጀግንነት ሰሌዳ ላይ በደማቁ የጻፈችበት እንዲሁም በርካታ ልጆቿ ለክብሯ ሲሉ የተሰውበት የሃዘንም፣ የደስታም፣ የድልም፣ የደምም፣ የልዕልናም ወር ነው የካቲት ለኢትዮጵያ፡፡
በጣሊያን ፋሽስት በግራዚያኒ ትዕዛዝ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን የተጨፈጨፉት በዚሁ በየካቲት ወር ነበር፡፡
ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት የካቲት 12 በኔፕልስ የጣሊያን ልዕልት መወለዷን አስመልክቶ የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያ አገረ ገዥ የነበረው ፊልድ ማርሽ ሮዶልፍ ግራዚያኒ በቀደመው ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስት ደስታውን ለመግለጽ ግብዣ አዘጋጀ፡፡
በወቅቱ የጣሊያንን አገዛዝን የተቃወሙት አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አሰግዶም በወረወሩት ቦምብ ግራዚያኒን ጨምሮ የጣሊያን ባለስልጣናት በመጎዳታቸው ምክንያት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና የደብረ ሊባኖስ መነኩሳት በመጨፍጨፋቸው በኢትዮጵያ ጠባሳ ታሪክ ትቶ አልፏል፡፡
የጥቁር ህዝቦች ኩራት፣ የኢትዮጵዊያን ድል የድሉም የደሙም ውጤት አድዋ በየካቲት ወር 1888 ዓ.ም ነበር በኢትዮጵያ የታሪክ ብራና በማይደበዝዝ ቀለም የተጻፈው፡፡
የካቲት 23 እለተ እሁድ ረፋዱ ላይ የጀመረው የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ቀኑን ሙሉ ምርኮና አስከሬን ሲሰበሰብ ውሎ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ድሉ ለጥቁሮች መሆኑ ሲበሰር ኢትዮጵያ በአፍሪካዊያን ላይ የነጻነት እና የተስፋ ብርሃን በጀብደኛ ልጆቿ ለኮሰች፡፡
አሁን የአለም ሃያላን አገራት ደረስንበት የሚሉት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ ተፎካካሪያቸውን የሚያሽቆለቁሉበት የፕሮፓጋንዳ ፍልስፍና በዚሁ በያዝነው በየካቲት ወር በአድዋ ጦርነት በባሻ አውአሎም የተተገበረ የቅድመ ኢትዮጵያዊያን እውቀት ነበር፡፡
በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጣሊያን ከምሽጉ እንዲወጣ የተዘጋጀው ነገር በኢጣሊያኖች የሚታመን በኢትዮጵያ ሰው በኩል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ከምሽጋቸው ወጥተው ውጊያውን እንዲጀምሩ ማድረግ ሲሆን ይህን ባሻ አውአሎም ታሪካዊ ገድል ፈጽሟል፡፡
ለበርካታ አመታት በድምቀት መዘከርን እና መታወስን የተነፈገው ሌላው የወርሃ የካቲት የኩራትና ድምቀት ታሪካችን የሆነው የካራማራ ድል ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት እንደ ሀገሪቱ አቆጣጠር የካቲት 26/1970 ቀን የተፈጸመ የኢትዮጵያዊያን ገድል ነበር፡፡
የሶማሊያ ጦር በምስራቁ እና በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ድንበር ጥሶ በመግባት ሉዓላዊ ግዛት ገንብቶ የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች በተለመደ ጀብዳቸው ግዛቱን ነጻ በማውጣት የሃገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በካራማራ ተራራ ላይ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል፡፡
ሃገሪቱ ታሪክ አትረሳም ውለታ አትዘነጋምና የተሰውላት ልጆቿን፣ የተዋደቁላት ጀግኖቿን፣ የሞቱላት አርበኞቿን ሃውልታቸውን በማሰራት፣ ገድላቸውን በማጋራት እና ታሪካቸውን በመዘከር የሰማዕታት ቀኑን በማርሽ ባንድ አጅባ፣ በፉከራ ጀብዳቸውን፣ በቅኔ ምጥቀታቸውን በጣዕመ ዜማ ትህትናቸውን ታስባለች፡፡
(በብርሃኑ አበራ)