የሱዳን ባለሥልጣናት ከህዝባዊ አመጹ ጋር በተያያዘ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ምክትል በቁጥጥር ስር አዋሉ

የካቲት 05/2013 (ዋልታ) – የሱዳን ባለሥልጣናት በሀገሪቱ ከሰሞኑ እየተባባሰ ከመጣው ህዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ምክትል እና ሌሎች ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ አካላትን በቁጥጥር ስር አውለዋል።

ሱዳን በተለያዩ ከተሞች የተስፋፋውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በ 7 ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አወጅ አውጃለች።

የሱዳን ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሀሳቦ ሞሃመድ አብደራህማን ናቸው፡፡

የቀድሞው ምክትል የታሰሩበት ምክንያት ሰልፈኞችን በበርካታ ግዛቶች ጎዳና ላይ እንዲወጡ አነሳስተዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

ህዝባዊ አመጹ በተስፋፋባቸው በተለይም ሰሜን ዳርፉር፣ በምዕራብ ዳርፉር ፣በሰሜን ኮርዶፋን እና በምስራቅ ዳርፉር ግዛቶች ንብረት የማውደም፤ሱቆች እና ገበያዎች የመዝረፍ እንቅስቃሴዎች ነበሩ መባሉን ሚዲል ኢስት ሞኒተርና ብሉምበርግ ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።