ኢትዮጵያውያን ከመከላከያ ጎን በመቆም የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋት ሴራ ማክሸፍ እንደሚኖርባቸው ተገለጸ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋት ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው የመከላከያ ሰራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

መርሃ ግብሩን “አንድነት ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት” ያዘጋጀው ሲሆን ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

ጀነራል መኮንኑ  አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ ታሪክ ይቅር የማይለው የሀገር ክህደት መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት የዜጎችን ደህንነትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተገዶ በገባበት የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ አንጸባራቂ ድሎችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ደህንነት አስጠብቆ ሰላምን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የደገሱትን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ ከመከላከያ ሰራዊቱና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደ “አንድነት ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት” አይነት ድርጅቶች ደግሞ ዓላማቸውን ከግብ እንዲያደርሱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ፕሬዘዳንት ጋዜጠኛ ሰለሞን ኃይለየሱስ፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ከነ ሙሉ ክብሯ እየጠበቀ ላለው ሰራዊት የሚደረገው ማንኛውም ድጋፍ ቢያንስ እንጂ አይበዛም ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊት አባላትንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡