ኢንስቲቲዩቱ ለሌማት ትሩፋት ዘመቻ መሠረት የሚጥል የዝሪያ ማሻሻያ ሥራ እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ልማት ኢንስቲቲዩት ለሌማት ትሩፋት ዘመቻ መሠረት የሚጥል የዝሪያ ማሻሻያ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሜቴው የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ልማት ኢንስቲቲዩት ከተሻሻሉ ከብቶች ዘረመል የማምረት፣ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቤተ-ሙከራን እና ፈሳሽ ናይትሮጅን የሚያመርተውን ማሽን ምልከታ አድርጓል።

ቋሚ ኮሜቴው ተቋሙ ሰው ሰራሽ የዝርያ ማሻሻያ ዘዴን በመጠቀም በስፋት ለመስራት፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና የሌማት ትርፋቶች ተጠናክረው እንዲሰሩ አስገንዝቦ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች፣ የማኔጅመንቱ አባላት እና ባለሙያዎች በእኔነት ስሜት ተቀናጅተው የሚሰሩትን ሥራ አድንቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የእንስሳት ሀብት ልማት ሥራ በዋናነት ከምግብ ዋስትና ባለፈ የምግብ ሉአላዊነት ለማስከበር እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ጭምር ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተው የእንስሳት ሀብት ልማት ከፍተኛ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መጨመር የሚችል እና ለሰው ልጅ የምግብ ዋስትና ጉልህ ሚና ቢኖረውም ቀደምሲል በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ገልጸዋል፡፡

የተቋሙ ዋና ተግባር የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል ከመሆኑ አንፃር ዝርያ ማሻሻል ላይ ካልተሰራ ትርጉም እንደሌለው አስገንዝበው ተቋሙ እንዲጠናከር ዝርያው የተሻሻለ ኮርማ፣ በቂ ንጥረ ነገር ያለው መኖ፣ በቂና ብቁ ተመራማሪዎች፣ አዳቃይ ባለሙያዎችና በየክልሎች ተጨማሪ የፈሳሽ ናይትሮጅን ማሽን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) ተቋሙ ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራት ለቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አስረድተው የተመራማሪዎች ጥቅማጥቅም ፓኬጅ እንዲፈቀድ፣ የርቢና የወተት ግብይት አዋጆች እንዲፀድቁ ጥረት በማድረግ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

የፈሳሽ ናይትሮጅን ፕላንትና የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ትኩረት እንዲያገኝ ቋሚ ኮሚቴ ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባና የሆለታ ማዕከል የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኝ እና ኢንስትቲዩቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር እንዲገባ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሊያግዘን ይገባል ማለታቸውን ምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።