ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2013 በጀት ዓመት 401 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
ኢንተርፕራይዙ የአዲስ አዳማ እና ድሬዳዋ ደወሌ የፍጥነት መንገዶች የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በ2013 በጀት አመት 8 ሚሊየን 925 ሺህ 529 ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ አቅዶ 8 ሚሊየን 856 ሺህ 1 የተሽከርካሪ ትራፊክ ፍሰት እንዳከናወነ ተገልጿል።
በዚህም የእቅዱን 99 በመቶ በማሳካት 401 ሚሊየን ብር ገቢ እንዳገኘ ጠቁሟል። ይህም ከባለፈው 2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ8 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።
ከገቢ ውስጥ 25 ነጥብ 89 ሚሊየን ብር የሚሆነው ከማስታወቂያ ቦታዎች ገቢ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ገቢ እንደተገኘ ነው የተገለፀው።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ 300 ኪሎ ሜትር የሚደርስ መንገድ የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በቀን በአማካኝ 26 ሺህ ተሽከርካሪዎች ፍሰት ያስተናግዳል ተብሏል።
ኢንተርፕራይዞች ከአዲስ አዳማ እና ድሬዳዋ ደወሌ በተጨማሪ የሞጆ ባቱ የፍጥነት መንገድ ርክክብ ሲደረግ በ2014 በጀት ዓመት 700 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱንም አመልክቷል።
የመንገዱን ደህንነት የተጠበቀ ለማድረግና ለተጠቃሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ በደህንነት ካሜራ የታገዝ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይም ተጨማሪ ዘመናዊ ተክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
(በምንይሉ ደስይበለው)