ኢዜማ ወደ ግንባር ለሚዘምቱ አመራሮችና አባላት ሽኝት አደረገ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ግንባር ለሚዘምቱ አመራሮችና አባላት በዛሬው ዕለት አሸኛኘት አድርጓል።

በሽኝት ወቅት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢዜማ ሊቀመንበር የሽዋስ አሰፋ አመራሩና አባላት ለሀገር ኅልውና ጥሪ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ ወደ ግንባር በመሄድ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅለው ለአገሩ እንደሚቆምና በድል አድራጊነት እንደሚመለሱም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከዚህ ቀደምም የኢዜማ አባላት ወደ ግንባር በመሄድ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸው ኢትዮጵያ የተከፈተባት መጠነ ሰፊ ዘመቻ በድል እስኪታጠናቅቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሽኝቱ ወቅትም የአባት እና የእናት አርበኞች የተገኙ ሲሆን ወደ ግንባር ለሚዘምቱ አመራሮችና አባላት የኢትዮጵያን ባንድራ ከአደራ ጭምር አስረክበዋል።

በሙባረክ ፋንታው