ኢዜማ የሕዳሴ ግድብ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ደስታውን ገለጸ

ኢዜማ

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ደስታውን ገልጿል።

ፓርቲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልእክት፣ “ኢዜማ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን በደረሰበት ደረጃ መያዝ የሚችለው የውኃ መጠን ሞልቶ በግድቡ አናት ውኃው መፈሰስ በመጀመሩ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል” ብሏል።

“ግድቡ በቀጥታ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጥቅም በላይ የሉዓላዊነታችን እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ምሳሌ ነው ሲልም” አክሏል።

ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አስተዋፅዖ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ያመሰገነው ፓርቲው፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል።