ኢዜአ ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍ 2 ሺሕ መጻሕፍትን አስረከበ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ካሉት 38 ቅርንጫፍ ጣቢያዎቹ ከሚገኙ ጋዜጠኞች ለሁለተኛ ጊዜ ያሰባሰበውን 2 ሺሕ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍ አስረክቧል።

መጻሕፍትን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያስረከቡት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ መጻሕፍቱ የኪነ ጥበብ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የተለያዩ ዋና ጉዳዮችን የያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሙዓዘ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለተደረገው የመጻሕፍት ስጦታ ምስጋና አቅርበው ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እያበረከተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ኢዜአ የአሁኑ መጻሕፍትን ጨምሮ በሁለት ዙር ከ7 ሺሕ 500 በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍ አበርክቷል።

በሱራፌል መንግሥቴ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW