ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ ሊካሄድ ነው

የካቲት 27/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን (ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

‘ኤችአር 6600’ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደኅንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።

ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት መክሰስ አላማም ያለው ሲሆን የቪዛና ጉዞን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል ያስቀምጣል።

‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት እንደሚካሄድ የኒውዮርክ ኒውጀርሲ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሰብሳቢ አክሊሉ ታፈሰ ገልጸዋል።

ሰልፉ ሕጉን ባረቀቁት የኒውጀርሲ የኮንግረስ አባል ቲም ማሊኖውስኪ የሚሰሩበት ቢሮ ፊት ለፊት እንደሚከናወንና እሳቸውንና ሕጉን የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።

ሕጉን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚቃወሙትና የኮንግረስ አባሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንደሚሰጣቸው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ረቂቅ ሕጉ ኤርትራንም የሚመለከት በመሆኑ በሰልፉ ላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኤርትራውያንም እንደሚሳተፉበት ዋና ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ረቂቅ ሕጉ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን የማስገንዘብ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ኢትዮጵያውያንም በአገር ውስጥ ሆነው የተቃውሞ ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ በመቃወም በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተስፋ ለኢትዮጵያ ከ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ) ፣ ኤርትራ አሜሪካውያን ብሔራዊ ምክር ቤትና ሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል ጋር በመተባባር ያዘጋጀው እንደሆነ ተገልጿል።