እርዳታ የምትሻው በቦክስ ለሀገሯ ወርቅ ያስገኘችው ቤተልሄም

በመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክላ የወርቅ ሜዳሊያ አምጥታለች፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የቦክስ ታሪክ የመጀመሪያዋ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሴት ቦክሰኛ አድርጓታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የማንዴላ ካፕ ውድድርም ለሀገሯ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡ ብርቱዋ ምክትል ሳጅን ቤተልሄም ገዛኸኝ፡፡

የሀገሯን ባንዲራ በእነዚህ መድረኮች ከፍ ያረገችው ቤተልሄም ዛሬ ላይ ግን በጉዳት ላይ ትገኛለች፡፡ በኦሎምፒክ ሀገሯን በድጋሚ ማስጠራት የምትፈልግ ቢሆንም የትከሻ ውልቃት አጋጥሟት በቤቷ ተቀምጣለች፡፡

ቤተልሄም ከአዲስ ዋልታ ጋር ባደረገችው ቆይታ ሁለቱም ትከሻዎቿ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው እንደተነገራት ገልጻለች፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው ገንዘብ ግን ለኔ የሚያስደነግጥ የምትለው ቦክሰኛዋ ለህክምናው አስከ 500 ሺሕ ብር እንደሚስፈልግ ተናግራለች፡፡

የቤተልሄም አባት ልጃቸውን ለማሳከም አቅም እንደሌላቸው በእንባ ታጅበው አስረድተዋል፡፡ “ሀገር አስጠርቶ አካል ጎድሎ ሲመለስ በጣም ያማል” የሚሉት አባቷ ለልጃቸው ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም እንደጀመርኩት ሀገሬን ማስጠራት ፍላጎቴ ነው ብላለች፡፡ ነገር ግን ህመሜ ፍላጎቴንና ምኖቴን እንዳላሳካ ሆኖብኛል ስትል ተናግራለች፡፡ የስፖርት አፍቃሪያንም ወደ ቀድሞ አቋሟ እንድትመለስ ድጋፍ አንዲያደርጉላት ጥሪ አስተላልፋለች፡፡