“እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ” በሚል በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ሁሉ አቀፍ ስፖርት ተካሄደ

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – “እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ” በሚል መሪ ቃል መከላከያ ሠራዊት ደጀንነቱንና አጋርነቱን ለመገለጽ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ሁሉ አቀፍ ስፖርት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነባት አደጋ ለመታደግ መላው የወላይታ ህዝብ ከጀግናው የመከላከያ ጎን መሆኑን የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ተናግረዋል።
ዶክተር እንድሪያስ በሀገራችን ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ለውጥ ከመጣበት ማግስት ጀምሮ ጁንታው የህወሃት ቡድን በህቡዕ በገሀድ ከሌሎች አፍራሽ ኃይሎች ጋር በመደራጀት ሀገራችን ለማፍረስ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም እኩይ ተግባሩ በጀግናው መከላከያ ሠራዊት ሊከሽፍ ችሏል ብለዋል።
ይህ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በወላይታ ሶዶ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዞኑ ባሉ በሁሉም መዋቅሮች ተግባራዊ በመሆን የሀገራችንን ሠላምና አንድነት ለማስጠበቅ በአካልና በአእምሮ ዝግጁ የሆነ ዜጋን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዶክተር እንድርያስ አክለውም “እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ” በሚል ወኔና ሀገራዊ አንድነት ለጀግው መከላከያ ሠራዊት ደጀንነቱንና አጋርነቱን ለመገለጽ ለሚደረገው ለማንኛውም ለገራዊ ጥሪ ጀግናው የወላይታ ህዝብ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አቶ ጌታቸው ገቡ የወላይታ ዞን ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እንዳሉት ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ልዩነት በስፖርታዊ እንቅስቃሴው ከመሳተፍ ባሻገር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያሳዩዩት ወገንተኝነትና ደጀንነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ሁሉም የስፖርቱ አፍቃሪያንና መላው ህብረተሰብ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለማበረታታት እና ለመደገፍ በሚፈለገው ሁሉ የበኩላችውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
የስፖርቱ ተሳታፊዎች እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ፤ የትም፣ መቼም፣ በምንም ሁኔታ ለሀገሬ እዘምታሁ በማለት የጋራ ድምጽ ያሰሙ ሲሆን በሃገር ሠላምና ደህንነት ላይ አደጋ የሚደቅን ማንኛውንም ጥቃትና ትንኮሳ ለመመከት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሶዶ ከተማ አመራርና እና ሠራተኞች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን መግለጣቸው የወላይታ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዘገባ ያሳያል።