እንከራከር እንወያይ እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም ፈጽሞ ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፈን አንስጥ – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጥቅምት 24/2015 (ዋልታ) እንከራከር እንወያይ እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም ፈጽሞ ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፈን አንስጥ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በአንድ ትልቅ ሀገር ይቅርና በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በልዩነቶቻችን ላይ እንነጋገር፣ እንወያይ አለፍ ሲልም እንከራከርባቸው እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፈን የምንሰጥ ባንዳዎች መሆን የለብንም ብለዋል፡፡
በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የተፈጸመበትን ሁለተኛ አመት አስመልክቶ ከአርባምንጭ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህዝብ ድምጽ የተመረጠው የብልጽግና መንግስት ብቻዬን ኢትዮጵያን ካልገዛሁ የሚል እብሪት ያለበት መንግስት አለመሆኑን ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ማንኛውም ሃሳብ ከመጣ ብልጽግና ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን መሰዳደብ፣ መገዳደል እና መገፋፋት ይብቃን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሁሉም ብሔሮች ተከባበረው እና ተደጋግፈው ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ሊደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
ስንዴ፣ ቡና፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ በጠቅላላው አረንጓዴ አሻራ ስንል የቆየን ሲሆን ዛሬ በአርባምንጫ አዲስ የልማት ዘመቻ በጋራ የምንጀምርበት ነው ሲሉ አብስረዋል፡፡
አርባምንጭ ልማቱ የሚታይባት እና ጸሎቱ የሚሰማባት ለምለም ከተማ በመሆኗ ዘመቻው የሚጀመርባት ከተማ እንድትሆን አስመርጧታልም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሰላምን ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ እና ለመላው ዓለም ህዝቦች ተመኝተዋል፡፡
በነስረዲን ኑሩ