እንግሊዝ በእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው

እንግሊዝ በእስራኤል የደህንነትና የፋይናንስ ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ማሰቧን የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ሰታመር ገለጹ።

እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል። ስብስባውን የጠሩት በጋዛ  የሰብዓዊ ሁኔታ  ላይ ለመወያየት መሆኑን የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታውቀዋል።

እስካሁን ለጋዛ የሰብዓዊ እርዳታ በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው ጋር የተነጋገርን ቢሆንም ጉዳዩ መፍትሄ ሳያገኝ ረጅም ጊዜ ወስዷል ብለዋል።

እስራኤል የንጹሃን ዜጎችን ጉዳት ማስቆም እንዳለባትና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞችም ስራቸውን እንዲሰሩ መፍቀድ እንዳለባት አሳስበዋል።

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ዴቪድ ላሚ እስራኤል የንጹሃን ዜጎችን ደህንነት መጠበቅና የነፍስ አድን እርዳታ የሚደርስባቸውን መንገዶች መክፈት እንደነበረባት ገልጸው የመንግስታቱ ድርጅት ስብሰባም በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደሚሆን መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።