እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም ነገር በፊት አገርን አስቀድመን የገጠመንን ፈተና በድል እንወጣለን – የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት

ጥቅምት 29/2014 (ዋልታ) እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም ነገር በፊት አገርን አስቀድመን የገጠመንን ፈተና በድል እንወጣለን ሲል የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

ከድል ዜና ጠባቂነት ወደ ድል ፈጣሪነት መሸጋገር እንደሚገባም የጋራ ምክር ቤቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ ገልጿል፡፡

“ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት  የገባችው ፈልጋ ሳይሆን ተገዳ እና ሰላምን ለማምጣት በመሆኑ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል” ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው፡፡

ከአሸባሪው ትሕነግ ጀርባ የመሸጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ድብቅ ጦርነት በመክፈት አገራችን ከድህነት አረንቋ ለመውጣት የምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ለማደናቀፍ ጦርነት የከፈቱ ቢሆንም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም ነገር በፊት አገርን አስቀድመን የገጠመንን ፈተና በድል እንወጣለን ብሏል መግለጫው።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነዋሪውን እና አባላቶቻቸውን በማስተባበር የኅልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

በተለይም የውትድርና ስልጠና እና አቅም ያለው ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት፣ በገንዘብ፣ በቁስ፣ ደም በመለገስ ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ ተነግሯል።

ማህበረሰቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ እና አጠራጣሪ ጉዳይዎች ሲያጋጥሙ ለጸጥታ ኃይል  እንዲያሳውቅ ጥሪ መቅረቡን ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡