ከ 12 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 83 በመቶ ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተገለጸ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) ግብርና ሚኒስቴር ፈታኝ የነበረውን የዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ በማለፍ በኢትዮጵያ ዓቅም ለመግዛት የታቀደው 12 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል 83 በመቶ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ገለጸ።
ይህም ዓምና ከተገዛው 14 ነጥብ 51 ሚሊየን ኩንታል ጋር ሲነጻጸር 1 ነጥብ 61 ሚሊየን ቅናሽ ያለው ሲሆን ምክንያቶቹም የዋጋ መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት እና የአቅራቢዎች ፍላጎት ውስንነት መሆኑን ሚኒስቴሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት አስረድቷል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛውን ልዩ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
በዚህም ግብርና ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት ያቀዳቸውን የዘርፉን ተግባራት፤ በሰብል እና ሆርቲካልቸር ልማት፣ በእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት፣ በግብርና ኢንቨስትመንት እና ግብዓት ግብይት፣ በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና አጠቃቀም፣ በሪፎርም ሥራዎች እና የተቋማት አመራር እንዲሁም በተያያዥ ጉዳዮች በምን ያህል ደረጃ እንዳሳካ፣ የገጠሙትን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች አስመልክቶ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን አማካኝነት ሪፖረቱ እየቀረበ ነው።
በሪፖርቱ በመኸር ወቅት 13 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 12 ነጥብ 8 ሚሊየን (97 በመቶ) በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 374 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 336 ነጥብ 60 (90 በመቶ) መሰብሰብ ተችሏል ተብሏል።
አፈጻጸሙ በምርት ደግሞ በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 341 ሚሊየን ኩንታል፤ በ5 ሚሊየን ኩንታል (1 ነጥብ 3 በመቶ) ማነስ ያሳያል ነው የተባለው።
ይህም የሆነው በግጭት ምክንያት ማምረት ያልቻሉ ዞኖች እና በትግራይ ክልል ላይ ያለው ሪፖርት ባለመካተቱ እንደሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።