ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ንብረቶችን ሰርቀው የተሰወሩ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ዋሉ

የካቲት 09፣ 2013 (ዋልታ) – በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በጥበቃ ስራ ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት ውስጥ ከሌሎች ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ንብረቶችን ሰርቀው የተሰወሩትን 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ/ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ክልል ልዩ ቦታው ስንቱ ህንፃ አካባቢ ነው።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚኪሊላንድ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተበበሪያ በተገኙነው መረጃ መሰረት 1ኛው ተጠርጣሪ በአይመን ሸኪብ የሽቶና ኮስሞቲክስ ማከፋፈያ የግል ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሰራ ተቀጥሮ የሚሰራ ሲሆን፣ ከሌሎች 2 ተጠርጣሪዎች ጋር በመተባበር ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ሽቶዎችን፣ ኮስሞቲክስ እና 1 ጀኔሬተር እንዲሁም 4 ካሜሪዎችን ሰርቀው ከተሰወሩ በኋላ የግል ተበዳይ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ባመለከቱት መሰረት የምርመራ ቡድን በማቋቋም ሁሉንም ንብረቶች ከነተጠርጣሪዎቹ በወንጀል ኢንትለጀንስ አባላት ብርቱ ጥረት ከገቡበት ገብተው በቁጥጥር ስር በማዋል ተገቢው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ባለድርጅቶችና ባለንብረቶች የጥበቃ ሰራተኞች ወደ ወንጀል ተግባር እንዳይገቡ አስፈላጊውን ትምህርት፣ድጋፍና ቁጥጥር አስቀድሞ በማድረግ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን መከላከል ተገቢ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስግንዝቧል፡፡