ከ1 ሺሕ 600 በላይ የሳይበር ጥቃቶች ሙከራ ከሸፉ

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በተለያዩ ተቋማት ላይ የተሞከሩ ከ1 ሺሕ 600 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

በአስተዳደሩ የሳይበር ጥቃት ትንተና ቡድን መሪ አቤል ተመስገን እንደተናገሩት ባለፉት ሦስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች አብዛኞቹ ዒላማቸው በፋይናንስና ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በሚኒስቴሮች ላይ ነው።

በኢትዮጵያ ሊደርስ የነበረውን አደጋ የማዳን አቅም እየጎለበተ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው የሳይበር ወንጀል ኢ-ተገማች በመሆኑ ሁልጊዜም መጠንቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተቋማት የራሳቸው የመቆጣጠሪያ ማዕከላት በማቋቋም የመከላከል ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም አስረድተዋል።

አስተዳደሩ የመንግስትና የግል ተቋማትን የማማከር አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።

ተቋማት የሳይበር ጥቃት በሚያጋጥማቸው ወቅት በአስተዳደሩ በኩል አስፈላጊውን ትንተና ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ተቋማት መሰል ጥቃቶች በሚያጋጥማቸው ወቅት በ933 ነጻ የስልክ መስመር ለአስተዳደሩ ሊያሳውቁ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ በተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰ መረጃ ሲያገኝ ጥቃቱን ማን አደረሰው፣ ከየት ነው የደረሰው፣ ምን አይነት ክፍተቶች በተቋማቱ እንደነበሩ ትንተና ይሰራልም ነው ያሉት ቡድን መሪው።

በሰበሰበው መረጃ መሰረት የደረሱ የሳይበር ጥቃቶችን በመተንተን ችግሩንም መፍታት እንደሚቻል ተቋማት ሊረዱት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡