ከ1 ሺሕ በላይ የሽጉጥ ጥይት ከ3 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

የሽጉጥ ጥይት

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) ከ1 ሺሕ በላይ የሽጉጥ ጥይት ከጤፍ ጋር በመቀላቀል ወደ አዲስ አበባ ያስገቡ 3 ተጠርጣሪዎችን ከእነ ጥይቱ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎችና ጥይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በተለምዶ አባ ጅፋር መስጊድ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኝ አንድ ቁርስ ቤት ውስጥ ነው ተብሏል።

መነሻውን ምስራቅ ጎጃም ደብረወርቅ ከተማ ያደረገ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 92916 አ/አ ኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና አሽከርካሪና ተባባሪዎቹ ጥይቱን ከጤፍ ጭነት ጋር በመቀላቀል ወደ አዲስ አበባ ካስገቡ በኋላ ከአንድ የግለሰብ ቁርስ ቤት ውስጥ ተጠርጣሪዎቹን ከ1 ሺሕ 100 የሽጉጥ ጥይቶች ጋር የአዲስ አበባ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፀረ- ሠላም ኃይሎች የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የሚያሴሩትን ሴራ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ ሙከራቸውን እያከሸፈ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ኅብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW