መጋቢት 18/2016 (አዲስ ዋልታ) በበጀት አመቱ ከ100ሺሕ ሔክታር በላይ አሲዳማ የእርሻ አፈርን ለማከም ከ1.5 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህን የገለፀው “የአፈር ጤና ለሀገር ህልውና” በሚል በሒልተን ሆቴል እያካሄደ በሚገኘው የ2016/17 የኖራ አቅርቦትና ስርጭት ሀገራዊ ማስጀመርያ ፕሮግራም ላይ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) መንግስት የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በማንሳት እስከ አሁን በተሰሩ ስራዎችም መልካም ውጤቶች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ይህን ለማሳካትም ከተለያዩ የግሉ ዘርፎች ጋር በጥምረት የሚሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚታረሰው አጠቃላይ መሬት 43 በመቶ የሚሆነው ወይም 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው ወይም 3.1 ሚሊየን ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡
በመሆኑም 105ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬትን ለማከም እንደሚሰራ ተጠቁሞ ከዚህ ውስጥም በኦሮሚያ ክልል 46 ሺሕ 116 ሄክታር የእርሻ መሬት፣ በአማራ 41ሺህ 570 ሄክታር የእርሻ መሬት በአመቱ የሚታከምባቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም ከ3.1ሚሊየን በላይ ኩንታል ኖራ የሚያስፈልግ ሲሆን ለዚህም ከ2.8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል ተብሏል።
የግዢ ሂደቱ 50 በመቶው በመንግስት ቀሪው 50 በመቶ በአርሶ አደሩ የሚሸፈን በመሆኑ ከመንግስት በኩል 1.5 ቢሊየን ብር ያህል መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፌደራል እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች የተወከሉ ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡
በታምራት ደለሊ