ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ማህበረሰቡን ተቀላቀሉ

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የአሥፈጻሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸማቸውን እየገመገመ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው የቢሯቸውን እና የተጠሪ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በዓመቱ የታቀደውን ዕቅድ ከመፈጸም ይልቅ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማርገብ ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረው የጸጥታ ችግሩ መደበኛ ዕቅዶችን ለመፈጸም እንቅፋት ኾኖባቸው መቆየቱን ነው የተናገሩት።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ክልሉን ዘርፈ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለውና ክልሉ በውጫዊ እና በውስጣዊ ችግሮች መፈተኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲቀጥል ማድረጉን ጠቅሰው የጸጥታ ኀይሉን መልሶ ከማደራጀት ባለፈ የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባታቸውንና በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ወገኖች የተሃድሶ ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ከሐምሌ 2015  ጀምሮ በጸጥታ ችግር ውስጥ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው በውጭ እና በውስጥ ኀይሎች ግፊት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትን ለማፍረስ ጥቃት መድረሱን ነው የተናገሩት።

የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የጸጥታ መዋቅርን ማጠናከር፣ የጸጥታ ኃይሉን ማሠልጠን እና መልምሎ እንዲደራጅ መደረጉንም ገልጸዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የመልካም አሥተዳደር ችግርን እንዲፈታ መሠራቱንም ተናግረዋል።

የሰላም እሴት ግንባታ እና ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የታቀደው ዕቅድ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱንም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የጸጥታ ተቋሙ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በማርገብ፣ አካባቢውን በማረጋጋት እና የክልሉ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመጣ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ገልጸዋል።