ከ29 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እየተሰራጨ  ነው ተባለ

የምግብ ዘይት

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) በሀገር ውስጥ የተመረተ ከ29 ሚሊየን 774 ሺሕ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ እየተሰራጨ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት የምግብ ዘይት አቅርቦትን ለማሻሻል ለሀገር ውስጥ አምራቾች የተመደበላቸው የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም ድፍድፍ ፓልም ዘይት ከውጭ አስገብተው በማጣራት ከ29 ሚሊየን 774 ሺሕ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት አምርተው እየተሰራጨ መሆኑ ገልጿል፡፡

ሸሙ የምግብ ዘይት ማምረቻ ድርጅት ከ9 ሚሊየን 943 ሺሕ ሊትር በላይ፣ አል ኢምፔክ ከ3 ሚሊየን 301 ሺሕ 630 ሊትር በላይ፣ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ማምረቻ ድርጅት 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር አምርተዋል ተብሏል፡፡

27 ሚሊየን 142 ሺሕ 416 ሊትሩ ለክልልና ለከተማ አስተዳደሮች የተመደበ ሲሆን 2 ሚሊየን 61 ሺሕ 920 ሊትሩ ለሀገር መከላከያ እንዲሁም 57 ሺሕ 92 ሊትር ደግሞ ለፌዴራል ማረሚያ ቤት ተመድቦ  እየተሰራጨ መሆኑ ተገልጿል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች የተመደበላቸውን ኮታ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በመመሪያ ቁጥር 002/2011 በተገለጸ የዋጋ ስሌት መሰረት ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ተደራሽ እንዲደረግ ማሳስቡን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡