ከ2ሺሕ በላይ ጥይት እና 68 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ታኅሣሥ 1/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በጋራ በሠሩት የተቀናጀ ሥራ ከ2ሺሕ በላይ የክላሽን ኮቭ ጠብመንጃ ጥይት እና በተሽከርካሪ አካል በድብቅ በተዘጋጀ ስፍራ ውስጥ ተጭነው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡ 68 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

2ሺሕ 475 የክላሺን- ኮቭ ጠብመንጃ ጥይቶች ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ሰፈረ ሰላም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው የገበያ ማዕከል መያዙን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ጥይቶቹን ሶስት ተጠርጣሪዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ከሚሸጡ የተለያየ አይነት ጨርቃ ጨርቆች ጋር በሲሚንቶ ወረቀት ተጠቅልለው በማዳበሪያ ተቋጥሮ በሰው ሸክም ሲንቀሳቀስ ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እግዚቢቱ ከነ-ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ መረጃ ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፅዮን ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መነሻውን ከባሕር ዳር ቀበሌ 14 ከሚባል አካባቢ  ባደረገው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-05467 አ.ማ በሆነ ተሽከርካሪ  የኋላ ፍሬቻ መብራቱ  ተነቅሎ  በተሽከርካሪው  አካል  በድብቅ በተዘጋጀ ስፍራ (ሻግ) ተጭነው ወደ አዲስ አበባ የገቡት 68 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር  ስር የዋሉ መሆኑንና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ  1 ተጠርጣሪ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የሽብርተኛው ጁንታ ቡድንን ተልዕኮ የተቀበሉ ተላላኪዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚያደርጉት ህገ-ወጥ ተግባርን በማክሸፍ ረገድ ኅብረተሰቡ ለፀጥታ  ኃይሉ የሚያደርገው ተባባሪነት የሚደነቅ በመሆኑ ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ የህብረተሰቡ ቀና ተባባሪነትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡