ከ3 ሺሕ በላይ ሃሰተኛ ብር ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መስከረም 5/2015 (ዋልታ) ከ3 ሺሕ በላይ ሃሰተኛ ብር ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ዲያስፖራ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን የፖሊስ አባላት በመደበኛ የወንጀል መከላከል ስራ ተመድበው ቁጥጥር እያደረጉ በነበረበት ወቅት የግለሰቦቹን ሁኔታ ተጠራጥረው ባደረጉት ፍተሻ በኪሳቸው ውስጥ ሀሰተኛ ብር ይዘው መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

ከአንደኛው ተጠርጣሪ ኪስ ውስጥ 7 ባለ ሁለት መቶ ሃሰተኛ የብር ኖት፣ ከሁለተኛው ተጠርጣሪ ኪስ ውስጥ 5 ባለ ሁለት መቶ ሃሰተኛ የብር ኖት እንዲሁም ከሦስተኛው ተጠርጣሪ ኪስ 4 ባለ ሁለት መቶ ሃሰተኛ የብር ኖት በአጠቃላይ 3 ሺሕ 200 ሃሰተኛ ብር ተይዞ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሃሰተኛ ብሮችን ለማዘዋወር እና የግል ጥቅማቸውን ብቻ አስበው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦች በኅብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙ ያስታወሰው ፖሊስ አሁንም በግብይት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ወንጀሉን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW