ከ300 በላይ የህንድ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ስራ መጀመራቸው ተገለጸ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ650 በላይ የህንድ ኢንቨስተሮች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት ስራ መጀመራቸውን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሽሪን ሮበርት ተናገሩ።

አምባሳደሩ ከሠመራ ዪኒቨርሲቲ አመራርና ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም ከህንዳውያና መምህራኖች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያንና የህንድ ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ የህንድ ባለሃብቶች ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፤ አገራቸው በኢትዮጵያ በተለየያዩ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መስክ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የትምህርት ልማት ዘርፉ ሌላኛዉ የኢትዮ-ህንድ ወሳኝ የግንኙነት መስክ መሆኑን ገልጸው፤ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን በህንድ እየተከታተሉ ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች በተጓዳኝ ህንድ በየአመቱ ለ50 ተማሪዎች ነጻ-የትምህርት ዕድል ትሰጣለች ብለዋል።

በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ 80 ህንዳውያንን ጨምሮ በርካታ ህንዳውያን መምህራን በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እያገለገሉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መሀመድ ኡስማን (ዶ/ር) በበኩላቸው ህንድ የኢትዮጵያን የትምህርት መስክ በመደገፍ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።