ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ከ475 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የጎዴ መጠጥ ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ተመርቋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ የግንባታውን ወጪ የፌደራል እና የክልል መንግስት እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ ሸፍነውታል።
ፕሮጀክቱ የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ውሃን በማጣራት ለመጠጥ ብቁ የሚያደርግ ሲሆን፣ በቀን 8369 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በማጣራት 140 ሺህ ለሚጠጉ የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ማቅረብ ይችላል ተብሏል።
በምረቃ ሥነስርዓት ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የውሃ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የወደፊት እቅድ ማሳካት የሚችል ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ መመረቅ መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የማጠናቀቅ አቅምን እንደሚያሳይም ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ፕሮጀክቱ መንግስት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ እውን እንደሚያደርግ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር አብዱል ካማራ በበኩላቸው፣ የታሰበው የልማት እቅድ እውን ሆኖ የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት መቀየር መቻሉ ለተቋማቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።