ከ7 ሺሕ በላይ ዲያስፖራዎች አርባምንጭና አካባቢውን ጎበኙ

ጥር 8/2014 (ዋልታ) የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ከመጡ ዲያስፖራዎች መካከል ከ7 ሺሕ በላይ እንግዶች አርባምንጭና አካባቢውን መዳረሻቸው ማድረጋቸው ተገለፀ።

ትናንት 45 ዲያስፖራ ኢንቨስተሮች በአርባምንጭ ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አባላት የአርባምንጭ የተፈጥሮ ደን፣ ከአርባ በላይ ምንጮችን እና የአዞ ራንቹን እንዲሁም የዶርዜ ባሕላዊ መንደርን ጎብኝተዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብርሃኑ ዘውዴ ዞኑ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች፣ ለግብርና አመች የሆነ እምቅ አቅም እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት ያሉበት በመሆኑ በጋራ ለመስራት በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጥቁር ሕዝቦችን ችግር መፍታት የሚቻለው በምጣኔሃብት መበልጸግ ሲቻል ነው ብለዋል።

አብዛኛው የአፍሪካ ሕዝብ በገጠር በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራ በመሆኑ የግብርና ምርትን ከገበሬው ወደ ሸማቹ የሚያቀርብ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት “አብረን እንስራ” በሚል ዘመቻ ጀምረናል ማለታቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽንጉዳዮች መምሪያ መረጃ አመላክቷል።