ከ73 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች ተያዙ


ሐምሌ 26/2013 ( ዋልታ) –
 ከሃምሌ 16 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ከ73 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ ከሀገር ሊወጡና ወደሃገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን የገቢ ኮንትሮባንድ 69 ሚሊየን 60ሺህ 381ብር፣ ወጪ ደግሞ 4ሚሊየን 458 ሺህ 313 ብር በድምሩ 73ሚሊየን 518ሺ 694 ብር ግምት አላቸው ነው የተባለው፡፡

ከኮንትሮባንድ ቁሶቹ መካከል የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ ወርቅ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ጫማ፣ ምግብ ነክ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮስሞቲክስ፣ ሲጋራ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ፣ መድኃኒትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ቱሉ ዲምቱ እና አቃቂ ቃሊቲ፣ ቶጎጫሌ፣ ቦምባስ እና ቀብሪበያ መስመር፣ ሞያሌ፣ ያቤሎ፣ ቡሌ ሆራ፣ መተማ፣ ጋላፊ፣ አሶሳና ጊዘን፣ ባሮ ቀላና ሆሌ፣ አርሲ ሮቤ፣ ሳንጃና ባህር ዳር፣ ነጌሌና ዶሎ ኦዶ ሀረር፣ ለገሀር፣ ደከር፣ ባቢሌ፣ ሀረዌ፣ ሀረማያ፣ ሀማሬሳ፣ ቂሌ፣ ድሬ፣ ደወሌ፣ ባቲ፣ ኮንሶ፣ ጪጩ፣ አርባምንጭ ከተማ መግቢያና መውጫ፣ ቡርጂ መስመር፣ ፋሻ መስመር፣ ወናጎ ከተማ፣ ኦሞራቴ እና ካራት ከተማ ኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙት በህብረተቡና በፀጥታ አካላት ትብብር እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ሚኒስቴሩ ምስጋና አቅርቦ ትብብሩ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡