ከ95 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኮንትሮባንድ እቃዎች

ታኅሣሥ 18/2014 (ዋልታ) ከ95 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ ክትትል 43 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 51 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል ብሏል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 13 ነጥብ 9 ሚሊየን፣ 11 ነጥብ 8 ሚሊየን እና 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ይዘዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን ኮንትሮባንድን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል ወርቅ፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ሕዝብ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡