ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጫናዎችን ለመመከት መፍትሄው የኢትዮጵያዊያን አንድነት ነው – ሕንዳዊያን ባለሃብቶች

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያዊያን ዓለምአቀፍ ጫናዎችን በመመከት ለሕዳሴ ግድብ ከዳር መድረስ በአንድነት መቆም እንደሚኖርባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ሕንዳዊያን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደውና አድገው በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩት ሚስተር ማዮር ኮታሪ እና ሃርሽ ኮታሪ የሕዳሴ ግድብን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ራሳቸውን እንደ ኢትዮጵያዊ የሚገልጹት ሕንዳዊያኑ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ አምራች ዘርፍ በጫማ፣ በምስማርና ሽቦ፣ በፕላስቲክና በተለያዩ ጥሬ እቃዎች ማምረት ላይ የተሰማሩ ናቸው።

የቦንድ ግዥና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሕዳሴው ግድብ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ማዮር ግድቡ በተለይም የአምራቹን ዘርፍ በማሳለጥ በሀገሪቷ መፃኢ እድል ላይ ትልቅ ተስፋ መሰነቁን ገልጸዋል።

የዓባይን ውሃ በአግባቡ አለመጠቀም ለኢትዮጵያ “ፈጣሪ የሰጣትን የተፈጥሮ ፀጋ እንደማባከን ሃጥያት ይቆጠራል” ነው ያሉት።

የሕዳሴው ግድብ በሁለት ዙር ውሃ መሞላቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፤ ይህም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት እንደሚሉት የውሃውን ፍሰት እንደማይቀንሰው በተግባር ማሳየቱን አክለዋል።

ግድቡ ሁለት ጊዜ ውሃ ሲሞላ ምንም አይነት የውሃ መቀነስ ባልታየበት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የታችኞቹን ሀገራት የሚጎዳ አለመሆኑን እያስረዳ ባለበት ወቅት የግብፅና ሱዳን ዓለም ዓቀፍ ጫና የመፍጠር ጥረት ምክንያተ ቢስ ነው ሲሉም ኮንነውታል።

በኢትዮጵያ ከ60 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የአምፖል ብርሃን የማግኘት እድል የለውም የሚሉት ሚስተር ማዮር የሕዳሴ ግድቡን እውን አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል ለኢትዮጵያዊያን መብትም ግዴታም በመሆኑ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሚስተር ሻርክ ኮታሪ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ለሚመጡ ጫናዎች ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀው ‘አንድነታችንንና ሠላማችንን ማስጠበቅ ነው’ ይላሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ማንነታቸው እንዳለ ሆኖ በሀገራዊ አንድነት ተሳስረው ችግሮችን መመከት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቶቿ መጠቀም እንዳልጀመረችና በተለይ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚሰሩ የሆቴል፣ የቱሪዝምና ተያያዥ ዘርፎች ባለሃብቶች መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል ሚስተር ሻርክ ኮታሪ።

በግብጽ የአስዋንን፣ የብራዚልና ሌሎችም ግድቦችን እንደጎበኙ የገለጹት ሚስተር ማዮርም ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት በዘለለ በቱሪዝምና በሌሎች የስራ ዘርፎች ከፍተኛ ጥቅም ልታገኝ እንደምትችል ተናግረዋል።