ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) – ከመተከል ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ይኖሩበት ወደነበረው ወረዳ በተመረጡ ማዕከል መመለሳቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከዞኑ ኮማንድ ፖስት፣ ከአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን ከተፈናቃዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ተፈናቃዮች ወደ ተዘጋጁ ማዕከላት ተመልሰው አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡
ተፈናቃዮች አሁን ላይ በአራት ማዕከላት ማለትም በዳንጉር፣ ቡለን፣ ድባጤ እና ማንዱራ ወረዳ መኖር መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
ወደ ማዕከላቱ ለተመለሱ ዜጎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ አቀባበል እንደተደረገላቸው ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡