ከማካድራ የቀጠለው የጭና ጭፈጨፋ

ጳጉሜ 4/2013 (ዋልታ) የሕወሓት የሽብር ቡድን በማይካድራ ያደረገውን ዘር ተኮር የንፁሃን ጭፍጨፋ ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር ጭና መፈፀሙን ያሳወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የሕወሓት የወጣት ክንፍ የሆነው ሳምሪ የተሰኘ ገዳይ ስብስብ ከወራት በፊት በማይካድራ የአማራ ብሔር ተወላጆችን እየለየ ከ1 ሺሕ በላይ ንፁሃንን መጨፍጨፉን ያስታወሱት የጽሕፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም፤ የሽብር ቡድኑ ከሰሞኑም በጭና ተመሳሳይ ጭፍጨፋ መፈፀሙን አብራርተዋል፡፡

በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በተፈጸመው ጭፍጨፋ እስካሁን ከ200 በላይ ንጹሀንን መጨፈጨፉን የገለጹት ኃላፊዋ ትክክለኝ ቁጥሩን ለማወቅ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሱዳን የስደተኛ መጠለያ ውስጥ የነበሩ የሽብር ቡድኑ አባላት ተመልሰው ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ አማራ ክልል ውስጥ መያዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በተያያዘ ዜና አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል መጠነ ሰፊ ጥቃት ደርሶበት ከተደመሰሰና የተረፈውም ጥሎ ከሸሸ በኋላ ስልታዊ ማፈግፈግ እንዳደረገ ሲገልፅ መሰማቱ የቡድኑ የተለመደ ውሸት ነው ተብሏል፡፡