ከሱዳን ወደ ጎንደር በሽፋን ሊገባ የነበረ 599 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መነሻውን ሱዳን ማግነን ግዛት ያደረገ ኮድ 3 የታርጋ ቁጥር 62519-አአ ሃይሱዝ (Isuzu) መኪና ባዶ ጀሪካኖችን ከላይ በሽፋን በመጫን ነበር 599 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦችን ጭኖ መዳራሻውን ጎንደር በማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ከመነሻው የመረጃ ጥቆማ ያገኙት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የመረጃ ኦፊሰሮች ህገወጥ የጦር መሳሪያው በምን መልኩ፣ እንዴትና በማን ወደ አገር ውስጥ እንደገባ የመለየትና የተሽከርካሪውን እንቅስቃሴ በብርቱ የመከታተል ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ተቋሙ ለዋልታ በላከው መግለጫ አስታውሷል፡፡
ከሱዳን ማግነን የተነሳው ተሽከርካሪ መተማ፣ አብርሃ ጅራ፤ ማይካድራ ሶሮቃ፤ ሳንጃ ወይንም ታች አርማጭሆ ከዚያም ላይ አርማጭሆ፤ ትክል ድንጋይ እያለ ጎንደር ከተማ ሊገባ ሲል ወለቃ በተባለ ቦታ ላይ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጀት በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ የተቀናጀና ጥብቅ ፍተሻም 599 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ከመኪናው እስፖንዳ ስር ሻግ ተሰርቷላቸው ከተደበቁበት መገኘታቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በህገወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው መቀጠሉንም አመልክቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል በወሰዳቸው እርምጃዎች የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ህብረተሰቡም ላደረጉት የተለመደ ትብብርና ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በቀጣይም እንዲህ አይነት ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችንም ሆነ በሂደቱ እየተሰተፉ ያሉ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡