ከበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን አገልግሎቱ ገለጸ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ከበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን ገለጸ፡፡

ከአርቲስት ቴዲ አፍሮ ልደት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ከፍቅር ያሸንፋል ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የደም ልገሳ መርኃ ግብር በትላንትናው ዕለት መካሄዱን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በትላንትነው ዕለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ 170 የሚሆኑ በጎ ፍቃደኞች ደም በመለገስ 170 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለዋልታ አረጋግጠዋል፡፡

ሆኖም ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮግራሙ እንደተከለከለ የሚሰራጨው መረጃ ከአውነት የራቀና የሰብዓዊ አገልግሎት የሆነውን የደም ልገሳ ፕሮግራም በሚጎዳ መልኩ እየተላለፈ ስለመሆኑ አንስተው መልእክቶች ተገቢነት የሌላቸው እና መስተካከል የሚገባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾችም በግል፣ በክለብ እንዲሁም በማኅበር ተደራጅተው በአካል ለማያውቋቸው ሰዎች ክንዳቸውን በፍቅር ዘርግተው ደማቸውን እያጋሩ ህይዎት እያስቀጠሉ ያሉ ጀግኖች ናቸው ያለው አገልግሎቱ በደም ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ስም ምስጋና አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ማኅበር እና አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በክረምት በጎ ፍቃድ ሥራ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ብቻ ከ33 ሺሕ ዩኒት ደም በላይ ለማሰባሰብ አቅዶ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለፉት ሦስት ቀናት ከ1 ሺሕ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም ኅብረተሰብ በበጎ ፍቃደኝነት ደም በመለገስ ደም የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ህይዎት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ደም ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች እያሰባሰበ ደኅንነቱ እና ጥራቱን በማረጋገጥ የደም ህክምና ለሚሰጡ የጤና ተቋማት ደሙን ተደራሽ በማድረግ በደም መፍሰስ ወይም በተለያዩ የጤና እክሎች የደም እጥረት ያጋጠማቸውን ዜጎች ህይዎት ለመታደግ ድልድይ ሁኖ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በአድማሱ አራጋው