ከቤት ውጣ ብላኛለች በሚል ምክንያት ሴት አያቱን የገደለው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ

የአዲስ አበባ ፖሊስ

መስከረም 4/2014 (ዋልታ) ከቤት ውጣ ብላኛለች በሚል ምክንያት ሴት አያቱን የገደለው ተከሳሽ በፅኑ እስራት መቀጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተከሳሽ ሮቤል ቴዎድሮስ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው ነሐሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቀጠና 5 ወጣት ማዕከል አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተከሳሽ ሮቤል ቴዎድሮስ የ79 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ከአባቱ እናት ጋር ይኖር የነበረ ሲሆን ከቤት ውጣ ብላኛለች በሚል ምክንያት ከምሽቱ 2፡30 ላይ አያቱን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ጭንቅላታቸውን በመዶሻ ደጋግሞ በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ፖሊስ ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን ለአቃቢ ህግ ልኮ ክስ እንዲመሰረትበት አድርጓል፡፡

የተከሳሽ ሮቤል ቴዎድሮስን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑን በማረጋገጡ በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ማሳለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW