የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤና የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች በ11 ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ሴቶች ጋር በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
“ከብር ለጀግኒት” በሚል መርህ ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ብቁና ተሳታፊ መሆን እንዲችሉ የሴቶችና ህፃናትን ችግሮችን ለመቅረፍና ልዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ጉዳዮች ለይቶ መፍትሄ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀ ውይይት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ውይይቱ በቀጣይ 6 ወራት ሊሰሩ ለታሰቡ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች የሚረዳና አቅጣጫ ለማሰቀመጥ የሚያግዝ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በከተማዋ የሴቶችን እና ህፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን በተለይም የሴቶችን የምክር ቤት ተሳትፎ ከ18 በመቶ ወደ 48 በመቶ ከፍ እንዲል ስለመደረጉና ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ የሴቶችን ተሳትፎ እንዲጨምር በርከታ ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል፡፡
“ደሰተኛ ቤተሰብ በአዲስ አበባ” በሚል በ2013 ከ3መቶ ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑና በከተማዋ በሚሰሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይም ለሴቶች ትኩረት መስጠት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ እና የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ የልማት አጀንዳ እንደሆነ በማመን ለሴቶችና ህፃናት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረገም ተገልጿል፡፡
(በህይወት አክሊሉ)