ከተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር ውጪ ነጋዴዎች ሽያጭ እንዳያከናውን ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ተገለጸ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የእሁድ ገበያ ማዕከላት ከተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር ውጪ ነጋዴዎች ሽያጭ እንዳያከናውን ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ገለጸ።

በንግድ ቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአዲስ አበባ ከተማ የበዓል ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ለማስቻልና ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ በ188 የእሁድ ገበያ ቦታዎች ግብይት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊት የእሁድ ገበያ ቦታዎች ቅዳሜና እሁድ ብቻ ግብይት የሚፈጸምባቸው መሆኑን አስታውሰው ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰትና የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር ሳምንቱን ሙሉ ቀናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በእነዚህ የእሁድ ገበያ ማዕከላት ላይ የሚቀርቡ ምርቶች እንዲጨምሩ በተለያዩ ዘርፍ ላይ ያሉ አምራቾች በቀጥታ በመሳተፍ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም የምርት አቅርቦት፣ ከዋጋና ከተደራሽነት አንፃር በተሰሩ ስራዎች በገበያው ላይ መረጋጋትን እየፈጠሩ መሆናቸውን አመልክተው ኅብረተሰቡ በየማዕከላቱ በተለጠፉ የዋጋ ዝርዝሮችን በመመልከት ግብይት እንዲፈጽም አሳስበዋል።

ከተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር ውጪ ነጋዴዎች ሽያጭ እንዳያከናውኑ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ የገለጹት ዳይሬክተሩ ኅብረተሰቡ ህገ ወጥ ግብይት ላይ የሚሳተፉ አካላትን በማጋለጥ ተባባሪ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ ያስገነባቸው የለሚ ኩራ፣ ኮልፌ እና የአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ የግብርና ምርት አምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል ምርቶች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በእነዚህ ማዕከላትም ባዛሮች ተዘጋጅተው ምርቶች ለኅብረተሰቡ እየተሸጡ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የኑሮ ውድነትንና የምርቶች ዋጋ መናርን ለመቆጣጠር እንዲሁም በምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር በምክትል ከንቲባ የሚመራ ግብርኃይል ተቋቁሞ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በአድማሱ አራጋው