ከተማ አስተዳደሩ በጉጂ ዞን በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ጥር 18/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን በድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚሆን ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡
 
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉጂ ዞን በድርቅ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም በድርቁ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እየሞቱ ላሉት ለከብቶችና እንስሳት የሚሆን የሳርና የመኖ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ ድጋፎችን ለዞኑ አስተዳደርና አባገዳዎች አስረክበዋል፡፡
 
ከንቲባዋ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ‹‹የዛሬው ድጋፍ ዋና ዓላማ አብረናቸው እንደሆንን ለማሳየትና ፍቅራችንን ለመግለፅ ነው›› ብለዋል፡፡
 
ጉጂ አንድም በድርቅ ሁለትም ደግሞ በፀጥታ ችግር እየተሰቃየ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አካባቢው ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ አንለያችሁም፤ ድጋፋችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
 
አካባቢው ሰላም ሲሆን ደግሞ መጥተን እንጎበኛችኋለን፤ ትልቅ የሆነውን ፍቅራችንንም እናንተ ጋር ማድረስ ይቻለናል በማለትም አክለዋል፡፡
 
የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደለ ኦዶ በበኩላቸው በዞኑ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ኅብረተሰቡ ከብቶቹ ግመሎቹና ፍየሎቹ እያለቁበት መሆኑን ገልፀው ማኅበረሰቡ አሁን አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
 
ላቀረብነውም አገራዊ ጥሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እጅግ ፈጣን ምለሽ ስለሰጠንም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
 
የጉጂ አባገዳዎችም ለከተማ አስተዳደሩና ድጋፉን ላስተባበሩ አካላት በሕዝቡ ስም ስጦታ ማበርከታቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!