ከተባበርን የማንወጣው መከራ፤ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም – አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
ከተባበርን የማንወጣው መከራም ሆነ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም ሲሉ የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ፡፡
የክልሉ መንግሥት በክልሉ ትላንት የተካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የሰልፉ ዓላማም በተለያየ ጊዜና ቦታ የንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውንና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም መንግሥትን የሚጠይቅ ነው።
በተለይም ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና አካባቢው በጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ኃይል የተከፈለውን የህይወት መስዋእትነትና የደረሰውን ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ምክንያት በማድረግ የተጠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሰልፉ ላይ የተገኘው ህዝብ ሀዘኑን በምሬት የገለጸ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግዛቸው፣ ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ በመሆኑ ለአስተባባሪዎችና ለተሳታፊው ህዝብ ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና በክልሉ መንግሥት ስም ገልጸዋል፡፡
ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአማራ ህዝቦች ችግር በሰልፍ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን በመረዳት ወጣቱና መላው ህዝብ ለዘለቄታዊ መፍትሔዎች ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያም ሆነ የአማራ ህዝብ ጠላቶች ለረዥም ዓመታት መጠነ ሰፊ ሴራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩበት ሁኔታ በገቢር የተገለጸበት ዘመን በመሆኑ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመተባበር እንዲሁም ሰከን ብሎ በመምከር ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ በደም ፍላት መፍታት አንችልም ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ያለን እንደመሆናችን ዴሞክራሲን መለማመድ ሲገባን የፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮችንና አንዳንድ ከሰልፉ ዓላማ ውጭ የሆኑ መልእክቶችን ይዞ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ሊቆም ይገባልም ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ምርጫን እናካሂዳለን እያልን ኢዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን ልናበረታታ አይገባም ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአጣየና አካባቢውን አሁናዊ ሁኔታ ያብራሩት አቶ ግዛቸው, የሸዋሮቢት ከተማ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ወደ ከተማው ተመልሶ በመግባት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ያለ መሆኑን አስታውሰዋል።
በአጣየ ከተማ ላይ የደረሰው ውድመት ግን ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪዎች ተመልሰው የሚያርፉበት መጠለያቸው በመውደሙ ምክንያት የመንግሥትን ድጋፍ ወደሚያገኙባቸው አጎራባች ከተሞች በጊዜያዊ መጠለያ ላይ የሚገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አካባቢው በአሁኑ ሰዓት ወደ መረጋጋት የተመለሰ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግዛቸው፣ እነዚህ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሰላም ናቸው የምንለው ግን በእነዚህ አካባቢዎች ተከባብሮ በሚኖረው ማኅብረሰብ መካከል ሰርጎ በመግባት ከተማ ያወደመውና ህዝብን የጨፈጨፈው ኃይል ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በአካባቢው የተቋቋመውን ኮማንድ ፖስት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን የሠጡ ሲሆን፣ ኮማንድ ፖስቱ የክልሉ አመራርም የሚሳተፍበትና በጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት በመሆኑ በሂደት የሚገጥሙ ጉድለቶችን በጋራ እያረምን ችግሩን በዘላቂነት የምንፈታበት እድል ሰፊ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ከተባበርን የማንወጣው መከራ፤ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም በማለት የትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች ይሁኑ መላው ህዝባችን የአማራን ህዝብ ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር የንፁሃንን ሞት እና አንግልት ለማስቆም በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ መልእክት ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡