ከታሪከ የምንረዳው ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠው በአሸናፊነት ማለፍ እንደሚችሉ ነው ሲል ኬንያዊው ጋዜጠኛ ገለጸ

ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆምቦ ኦንያንጎ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) “ከታሪከ የምንረዳው ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠው በአሸናፊነት ማለፍ እንደሚችሉ ነው” ሲል ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆምቦ ኦንያንጎ ገለጸ።

“ኬንያዊያን የጎረቤት አገራቸው ኢትዮጵያን ሰላም፣ ደህንነትና ብሄራዊ አንድነት አጥብቀው ይፈልጋሉ” በማለትም ተናግሯል።

ከኢዜአ ጋር የበይነመረብ ቆይታ የነበረው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆምቦ ኦንያንጎ “የኬንያ ህዝብና መንግስት ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማትን ችግር እንድትወጣ ከጎኗ ሆነው ያግዛሉ” ብሏል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ችግር የኬንያ መሆኑን የተገነዘቡት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መፍትሄ በሚፈለግበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር መምከራቸውን አስታውሷል።

“የኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ ወዳጅነት ከጆሞ ኬንያታ እና ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ያለ ነው” የሚለው ጆምቦ ኦንያንጎ፤ ሁለቱ አገራት ወደፊትም ይህን የመተባበር እና የመደጋገፍ ባህላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያለውን ጠንካራ እምነት ገልጿል።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ሌሎች ኬንያውያን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የዚሁ ታሪካዊ ትስስር አካል እንደሆነም ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ በብዙ መልኩ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር መሆኗን የሚገልጸው ጋዜጠኛው፤ ወቅታዊው ችግር በቅርቡ እንደሚፈታ ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል።

ኬንያ እንደ የወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባልነቷ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጓቸው ጫናዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ እንዲሆን ደጋግማ አቋሟን እንደገለጸችም አስታውሷል።

“ከታሪከ የምንረዳው ኢትዮጵያውያን ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠው፤ ፈተናዎችን በማለፍ በአሸናፊነት መወጣት ይችላሉ” ያለው ጆምቦ ኦንያንጎ፤ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን መደገፍ ያለባቸው ከዚህ አንጻር መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

“ኢትዮጵያውያን የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ መደገፍ ከምዕራባውያንም ይጠበቃል” ብሏል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በጫና ወይም በማዕቀብ የሚፈታ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን በሚፈቱበት ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

ኬንያ ኢትዮጵያን የመደገፍ ሃላፊነት እንዳለባት የሚገልጸው ጋዜጠኛው “ይህም ሁለቱ አገራት በህዝብ ለህዘብ ግንኙነት የተሳሰሩ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያላቸውና በአህጉሪቱ ደረጃም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸው እንዲተባበሩ ያደርጋቸዋል” ሲል አብራርቷል።