ከቻግኒ መጠለያ ጣቢያ ወደ መተከል ዞን የተመለሱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ በሚያስችሉ አካባቢዎች ማረፋቸው ተገለጸ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – ከአዊ ዞን ቻግኒ መጠለያ ጣቢያ ወደ መተከል ዞን የተመለሱ ተፈናቃዮች ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ ሠብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ማድረስ በሚያስችሉ ምቹ አካባቢዎች እንዲያርፉ መደረጉን የድባጤና ቡለን ወረዳ አስተዳዳሪዎች ገለጹ።

ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋምና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በመተከል በግጭት ሳቢያ የደፈረሰውን ሠላምና ደህንነት ለመመለስ በዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ቻግኒ ራንች መጠለያ ጣቢያ የቆዩ ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በመጠለያ ጣቢያው ለተፈናቃዮቹ ሲደረግ የቆየው ሠብዓዊ ድጋፍ በሚኖሩበትም ወረዳ ተደራሽ እንደሚደረግ ያረጋገጡት የኮማንድ ፖስቱ የቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ ናቸው።

የአማራና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የሰነድ ርክክብ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የድባጤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ዋዊያ፤ በዞኑ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለመመለስ በርካታ የሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የመጠለያ ድንኳን ግንባታ፣ የማብሰያና የመጸዳጃ ቤት ዝግጅት፣ የጤናና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ መሰረተ ልማቶች መሟላታቸውን ጠቅሰዋል።

የቡለን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ነሲ በበኩላቸው፤ ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ዜጎች የተዘጋጀው ማረፊያ ቦታ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅና ማኅበራዊ አገልግሎት በቅርበት ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብም ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ አስተማማኝ ሠላም እስከሚሰፍን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲሆን እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በግብርናና ሌሎች የልማት ስራዎች በመሰማራት ስራዎችን የሚከውንበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ከመከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ያለ አንዳች የደህንነት ስጋት ኑሯቸውን እንዲመሩ እንደሚደረግም አክለዋል።

በየደረጃው ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል ልዩ ተልዕኮ በመስጠት ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስተማማኝ ጥበቃ እንደሚደረግ ተገልጿል።