ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግድ ማህበረሰብ እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያው ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሐምሌ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የፋይናንስ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተገኙበት ከንግድ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተግባራዊ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱ አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በዋነኛነት ዘላቂ ልማትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት፣ የመንግስትን የእዳ ጫና ለመቀነስ፣ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ተኪ ምርቶችን በማምረት፣ ለውጪ ገበያ የሚላከውን ምርት በማሳድግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር  እና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመፍጠር የውጪ ምንዛሬን ለማሳደግ እድል የሚፈጥር መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

የፋይናንስ ሚኒስትር ዲኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ማሻሻያውን ተከትሎ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር ደሃው እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ እንዳይጎዳ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ መጨመር፣ ደሃውን መደጎም ፣ በተለይም በሴፍቲኔት የታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ገቢ በሚያስገኝ መልኩ መደገፍ እና የስራ እድልን መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር  ስለመሆኑ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡

“በቀጣይም ከአምራቾች እና አስመጪዎች ጋር በቅርበት በመስራት እንዲሁም ገበያውን የሚያዛቡ፣ በተለይም ምንም ከውጪ ምንዛሪ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ የምንሰራ ይሆናል” ብለዋል ከንቲባዋ።