ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት መርቀው ከፈቱ

ሰኔ 26/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት መርቀው ከፍተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በመደበው 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት የተሰራና በቀን 86 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማምረት የሚችል ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውሃ ማምረቻው እያንዳንዳቸው ከ2 ሺሕ እስከ 5 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው 16 ጥልቅ ጉድጓዶች ያሉት ሲሆን በተጨማሪም 10 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታን የያዘ ነው።

ፕሮጀክቱ የ12 ኪሎ ሜትር ዋና የውሃ መስመር፣72 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሰባሰቢያ መስመር፣ 99 ኪሎ ሜትር የስርጭት መስመር ዝርጋታ አካቷል፡፡

ሁለት ግዙፍ የግፊት መስጫ ጣቢያዎች እና 38 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድን፣ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እና በጉድጓዶቹ አካባቢ የሚሰሩ የሲቪል ስራዎችን አኳቷል።

ይህ ፕሮጀክትም የከተማ አስተዳደሩን በቀን ውሃ የማምረት አቅሙን ከ674 ሺሕ ወደ 760 ሺሕ እንደሚያሳድገው ተገልጿል፡፡