ከንቲባዋ በቀን ከ288 ሺሕ በላይ እንጀራ የሚያመርት ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ የእንጀራ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ፋብሪካው 1000 ሺሕ የእንጀራ ምጣድ የሚኖረው ሲሆን እስከ 4 ሺሕ ለሚደርሱ እናቶችና ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር እና በ3 ወር ውስጥ ተገንብቶ ወደ ስራ እንደሚገባ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ፋብሪካው በቀን እስከ 3.4 ሚሊዮን በዓመት እስከ 1.3 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያመነጭ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ግዙፍ የእንጀራ ፋብሪካ የግብይት ሰንሰለቱን ጠብቆ በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች የጤፍ ምርት በመግዛት የሚጠቀም ሲሆን የእንጀራ ምርት ለዓለም አቀፍ ገበያ ኤክስፖርት ለማድረግም በእቅድ ተይዟል ተብሏል፡፡

ፋብሪካው እንደ ማሰልጠኛ የሚያገለግልም ሲሆን ሴቶች ራሳቸውን እየቻሉ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ክህሎት እያስጨበጠ እንደሚቀጥል ተመላቷል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ‹‹ይህ ፕሮጀክት የ2015 ዓ.ም የገና በዓል ለእናቶች የተበረከት ሥጦታ ነው›› ብለዋል፡፡

እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ብለን የጀመርነው ስራ ያለ እንጀራ ሌማት ሊሞላ አይችልም ነው ያሉት፡፡ የሚሠሩ እጆች እንዲበረክቱ በማድረግ እና በዙሪያችን ያልተጠቀምንባቸው ፀጋዎችን በመጠቀም መለወጥ የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉም መናገራቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡