ከንቲባዋ እና የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዱባይ ላይ በተዘጋጁ ሁለት ዓለም ዐቀፍ ጉባዔዎች ላይ ተሳተፉ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዱባይ ላይ የተዘጋጁትን የዓለም መንግሥታት ሰሚት 2022 እና የሴቶች ተሳትፎ በመንግሥት አመራርነት ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል።
ከመጋቢት 19/2014 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደው ጉባኤ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ከ1 ሺሕ 500 በላይ የመንግሥታት መሪዎችና ዓለም ዐቀፍ የእርዳታ ድርጅት አመራሮች በኢኮኖሚ፣ በከተማ አስተዳደር፣ በማኅበራዊ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንት፣ የሴቶች ተሳትፎ በመንግሥት አመራርነት እና በኮሙዩኒኬሽን ዙሪያ የተማከሩበት መድረክ ነበር።
በተጨማሪም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፕሪቲ ሲንሃ እና ከየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የማኅበራዊ ልማት ሚኒስትር ኤሳ ብሁመይድ ጋር የሁለትዮሽ ትብብር ሥራዎችን በጋራ ስለመስራት መወያየታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።