ከአማራና አፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በለንደን ተካሄደ

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያን እናድን” በሚል መሪ ቃል ከአማራና አፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በለንደን ተካሄደ፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከ“Defend Ethiopia” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል ጋር በጋራ በመተባበር በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በርካታ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ከውጭ የአገራችን ጠላቶች ጋር በማበር በአገራችን አንድነት ላይ የደቀነውን ኢትዮጵያና የማፍረስ እኩይ ተግባር ለመመከት በቁጭት ተነስተን ባገኘነው የድል መንፈስ ሆነን የገቢ ማሰባሰቢያውን አሰናድተናል ብለዋል።

አምባሳደር ተፈሪ አክለውም የረጅም ዘመን ታሪክና ባለጸጋ የሆነችውን አገራችንን ለማፍረስ በሽብርተኛው የሕወሓትና የሸኔ ፊታውራሪነት የተጠነሰሰው ሴራ መክሸፉን ገልጸው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙኃን እና የአንዳንድ መንግሥታት የሀሰት ትርክት ወርጅብኝን በኢትዮጵያዊያን ትግል ተቋቁመናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በገጠማት የህልውና አደጋ ጠላትና ወዳጆችዋን የለየችበት አጋጣሚ ነው ያሉት አምባሳደር ተፈሪ በተለይም ደግሞ አፍሪካዊያን በመላው አለም በተካሄደው የበቃ አለም አቀፍ ትግል በመሳተፍ ላሳዩት ያልተቋረጠ ድጋፍ ልናመሰግናችው ይገባል ብለዋል፡፡

የ“Defend Ethiopia” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል አስተባባሪ ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መስዋእትነት አንገታችንን ቀና አድርገን አድርገውናል።

በእንግሊዝ ለተፈናቀሉ ወገኖች እስካሁን 370 ሺሕ ፖውንድ በላይ መሰብሰቡን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡