ነሃሴ21/2013(ዋልታ) – ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በህገወጥ መንገድ ሊሄድ የነበረ ከ49 ሺህ በላይ ዶላር ኮምቦልቻ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የሽብርተኛው ህወሃት የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሰጧቸውን ተደጋጋሚ የሰላም ዕድሎች መጠቀም ተስኗቸው እየፈፀሙ ያሉትን ትንኮሳና ወረራ እንደ ሽፋን በመጠቀም አንድ አንድ አካላት ህግወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እየሞከሩ ነው ፡፡
እነዚህ አካላት የህዝባቸውንና የሀገራቸውን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከደህንነትና የፀጥታ አካላት እይታ ውጭ መሆን አልቻሉም፡፡
ከእነዚህ አካላት ውስጥ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴ ተጠርጥሮ ትናንት ምሽት ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለውን ዓሊ መሀመድ አደምን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ዓሊ መሀመድ አደም ኮንቴነሮችን ከጅቡቲ አዲስ አበባ የሚያመላልስ የከባድ መኪና አሸከርካሪ ነው፡፡
ግለሰቡ በቀን ነሃሴ 20/2013 ዓ.ም ማለዳ ላይ መደበኛ ስራውን ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ጅቡቲ ለማምራት ከመጀመሩ በፊት በህገወጥ ጥቅም ከተሳሰረው ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ጎራ በማለት 49 ሺኅ 300 ዶላር በሚስጥር በመቀበል ወደ ጅቡቲ የሚያደርገውን ጉዞ ይጀምራል፡፡
ዓላማውም ገንዘቡን ወደ ጅቡቲ በማጓጓዝ በጥቁር ገበያው በከፍተኛ ምንዛሬ በመቸብቸብ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡
ይሁንና ግለሰቡ በብሄራዊ መረጃና ደህንነትአገልግሎት ክትትል ሲደረግበት ስለነበር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ትናንት ከምሽቱ አምስት ሰአት ገደማ አካባቢ ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው ዓሊ መሀመድ አደም አድርስልኝ ካለውና አዲስ አበባ ከሚኖረው መተዳዳሪያውን ህግወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ካደረገው ግለሰብ የገንዘብ ጉርሻ በመቀበልና ተባባሪ በመሆን ጅቡቲ ለሚኖር ሌላ ተቀባይ አካል የአድራሽነት ሚና እንዳለው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡