ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የባይደን አስተዳደርን አየሞገቱ ነው

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመጠየቅ ያሰበው የአሜሪካ ሕግ ረቂቅ ውድቅ ተደረገ።
የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊን ሲቪክ ካውንስል ትላንት ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ስብሰባ መሰረት ሴናተር ጂም ኢንሆፌ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመጠየቅ በሴኔት ቢሮ የታሰበው “HR 4350” ውስጥ አንቀፅ 6464 እንዲሰረዝ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል።
የሲቪክ ካውንስሉ ፕሬዝዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ለሴኔተር ጂም ኢንሆፌ “የክፉ ቀን የቁርጥ ወዳጃችን ነዎት እና በመላው የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን እንዲሁም በዲያስፖራ ደጋፊዎቻችን ስም እጅግ እናመሰግናለን” ሲሉ ለሴናተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የወዳጅ አገራት ዜጎች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበርና ጫናዎችን ለማቃለል ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ።
በሌላ ዜና የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ኬረን ባስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ከአግዋ (AGOA) ያገዱበትንና ከ2 ሳምንት በኋላ የሚተገበረውን ውሳኔ እንዲሽሩ እያግባቡ መሆኑን አሳውቀዋል።
የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን እንዳያግድ የሚቻለኝን ያህል እየሰራሁ ነው፣ ተስፋም አለኝ ሲሉ ለኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን የሲቪክ ካውንስል አረጋግጠዋል።
“በድንገት የተላለፈው ውሳኔ ዜጎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማምጣት በቀር ለሰላሙ ምንም አማራጭ አይሰጥም” ያሉት የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ካረን ባስ የባይደን አስተዳደር ውሳኔ የኢትዮጵያ ሕዝብና መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ አሜሪካዊያን ደክመው ያመጡትን የምጣኔ ሃብት እድገት ከመቀልበስ ያለፈ ፋይዳ የለውም ሲሉ ተቃውመውታል።