ከኢድ እስከ ኢድ ምዕራፍ ሁለት ጥሪን ተከትለው ለገቡ የሙስሊሞች ማኅበር አባላት አቀባበል ተደረገ

ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው በድር የኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ የሙስሊሞች ማኅበር አባላት ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ምዕራፍ ሁለት ጥሪን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው።

አባላቱ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢድ እስከ ኢድ ሴክሬታሪያት አስተበባሪ መሀመድ እድሪስን (ፒኤችዲ) ጨምሮ የተለያዩ አካላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለማኅበሩ አባላት የተደረገው አቀባበል ከኢድ እስከ ኢድ ምዕራፍ ሁለት መርኃ ግብር በይፋ መጀመሩን እንደሚያበስር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ፒኤችዲ) በበኩላቸው በድር ኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ የሙስሊሞች ማኅበር 22ኛ ኮንቬንሽኑን ‘በድር ወደ ማንነት’ በሚል መሪ መልዕክት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለማካሄድ በመምጣቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ኮንቬንሽኑ ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ለማካሄድ ከታቀዱ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮንቬንሽን መካሄድ ኢትዮጵያን የማያውቁ ሁለተኛ ትውልድ ወጣቶች ከሀገራቸው ታሪክ ጋር የሚተዋወቁበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡